ማዲያት
ማዲያት ምንድነዉ?
ማዲያት በአብዛኛዉ ጊዜ በተወሰኑ የፊት ቆዳ ክፍሎች ላይ ቡኒ ወይም ጠቆር ያለ ቀለም ኖሮት ወጣቶች እና ጎልማሶች ላይ የሚከሰት ችግር ነዉ፡፡ ከተወሰኑ ወንዶች ዉጪ በአብዛኛዉ ሴቶች ላይ ይወጣል፡፡ እስከ 50 በመቶ የሚሆኑ ቶች በእርግዝና ጊዜ ይኖራቸዋል፡፡ ከነጮች እና ጥቁሮች ይልቅ እንደኛ ሃገር ባሉ ሰዎች ላይ ይብሳል፡፡
የማዲያት መንስዔ ምንድነዉ?
ማዲያት ባለባቸዉ ሰዎች ላይ ለቆዳ ቀለም የሚያመርቱ ሕዋሳት ከመጠን በላይ ቀለም (ሜላኒን) ያመርታሉ፡፡ ይህ ቀለም ሲባዛ ማዲያት ይሆናል፡፡ ይህንን ቀለም ከመጠን በላይ እንዲመረት ከሚያደርጉ ነገሮች ዉስጥ የሆርሞን መዛባት (እርግዝና፤ የወሊድ መቆጣጠሪያ መዉሰድ፤ የሆርሞን ሕክምና መዉሰድ)፤ አንዳንድ መድሐኒቶች (ለምሳሌ፡- የሚጥል በሽታ መድሐኒቶች)፤ የፀሐይ ጨረር፤ ጭንቀት፤ የጨጓራ ባክቴሪያ፤ የታይሮይድ በሽታ እና የመሳሰሉ ምክኒያቶች ይነሳሉ፡፡
የማዲያት ምልክት ምንድነዉ?
ማዲያት በዙሪያዉ ካለ ቆዳ ይልቅ ጠቆር ወይም ቡናማ በመሆን በጉንጭ፤ አገጭ፤ አፍንጫ፤ የላይኛዉ ከንፈር እና ግምባር ላይ ይወጣል፡፡ አንዳንዴም ለፀሐይ የተጋለጡ እንደ አንገት እና እጅ ላይ ይከሰታል፡፡
ከመልክ ልዩነት ዉጪ ማዲየት አያሳክክም፤ አያቃጥልም፤ ወደ ከፋ በሽታም አይቀየርም፡፡
መልክ ከማበላሸቱ ጋር የሚያመጣዉ የስነ-ልቦና ጫና ምንድነዉ?
በባህላዊ አስተሳሰብ ማዲያት ትዳር ወይም በአጠቃላይ ኑሮ ባለመመቸቱ የመጣ ችግር አድርጎ የማየት የተሳሳተ አመለካከት አለ፡፡ ሁለተኛ በፊት የነበረዉን መልክ በተወሰነ መልኩ ስለሚያበላሽ ሰዉ ሁሉ በሚያየዉ የፊት ቆዳ ላይ በመዉጣቱ ብዙዎች ደስተኛ አይሆንም፡፡ ይህ ዉሎ እያደረ ወደ ማፈር፤ መሸማቀቅ፤ ከማህበራዊ ሕየወት መራቅ እንዲሁም ድብርትን ያስከትላል፡፡
ማዲያት በሕክምና ይድናል?
ማዲያትን በመድሐኒት ማዳን እጅግ ከባድ ነዉ፡፡ ምክኒያቱም ቀለሙ በመድሐኒት ቢጠፋም ወይም ቢፈዝም ዋናዉ መሰረታዊ ችግር እስካልተፈታ ድረስ መመለሱ አይቀርም፡፡
እጅግ ብዙ የሆኑ የሕክምና ምርጫዎች ቢኖሩም፤ መድሐኒቶቹ በተቋረጠ ጊዜ ማዲያቱ የመመለስ እድሉ በጣም ሰፊ ነዉ፡፡ ነገር ግን እያንዳንዱ መድሐኒት የራሱ የሆነ የጎንዮሽ ጉዳት ስላለዉ በሐኪም ቢመረጡ መልካም ነዉ፡፡
መድሐኒቶቹ የሚተሉትን ይጨምራል፡-
- ፀሐይን መከላከል፤ የፀሐይ መከላከያ ቅባቶችን መቀባት
- ቆዳ የሚያነጡ መድሐኒቶችን (Hydroquinone፣ Retinoid creams፤ azelaic acid, ascorbic acid፤ kojic acid… ) እና ቆዳ እንዳይቆጣ የሚረዱ መድሐኒቶች (ቀለል ያሉ ኮርቲኮስቴሮይዶች - ነገር ግን በጥንቃቄ ከሌሎች መድሐኒቶች ጋር መጣመር አለባቸዉ)
- እንደ ኬሚካል ፒል (Chemical peels) ፤ ሌዘር እና Microneedling የሕክምና ዘዴዎችን መጠቀም
- List Item #3
- በተለያዩ ሜካፖች መሸፈን (Skin camouflage)
- አዳዲስ ተስፋ ሰጪ የሚዋጡ መድሐኒቶች እየተመረቱ ነዉ
ማዲያትን እንዴት እንከላከል?
- ዋነኛዉ ጥንቃቄ ከፀሐይ መጠበቅ ነዉ፡፡ ጥላ ስር መሄድ፤ እኩለ ቀን ላይ ብዙ አለመንቀሳቀስ፤ የሚያነፀባርቅ መስታወት እና ዉሃ ፊት አለመሆን፤ ሰፋፊ ኮፍያዎችን ማድረግ፤ ፀሐይን የሚከላከሉ ትላልቅ መነፅሮችን መጠቀም፤ እና የፀሐይ መከላከያ ቅባቶችን በአግባቡ መቀባትን ይጨምራል፡፡ ይህን ማድረግ ማድያቱ እንዳይሰፋ እና በሕክምና ከተሻሻለ በኋላ እንዳያገረሽ ይረዳል፡፡
- ጭንቀት መቀነስ
- የሚዋጡ የወሊድ መቆጣጠሪያ እንክብሎችን ወደ ሌላ ኢስትሮጅን ወደ ሌለዉ መቀየር
- የታይሮይድ ሆርሞን ችግር ካለ መታከም