Public Awareness
ለምጽ
ለምፅ (Vitiligo) ምንድነዉ?
ለምፅ ለቆዳችን ቀለም የሚያመርቱ ሕዋሳት በመጎዳታቸዉ ምክኒያት ቆዳችንን ነጭ በማድረግ የሚታወቅ በሽታ ነዉ፡፡ በማንኛዉም እድሜ የሚከሰት፤ በንክኪ የማይተላለፍ እና እስከ 1 በመቶ የሚሆነዉን የህብረተሰብ ክፍል ሊያጠቃ የሚችል የቆዳ በሽታ ነዉ፡፡ለምፅ ጤናችንን በቀጥታ ከመጉዳት ይልቅ በበሽታዉ በመያዛችን የሚደርስብን አዕምሯዊ ጫና ይበልጣል፡፡
ለምፅ በአካላዊ ንክኪ እና በዘር ይተላለፋል?
ለምፅ በንክኪ ፈፅሞ አይተላለፍም፡፡ በመሳሳም እና በግኑኝነትም አይተላለፍም፡፡
የለምፅ ምልክቶች ምንድናቸዉ?
በአብዛኛዉ ሰዉ ላይ ነጭ የሆነዉ ቦታ አያሳክክም፤አያብጥም፤ አያቃጥልምም፡፡ በመጠኑ ከትንሽ ክብ ነጭ ሽፍታ ጀምሮ ሙሉ አካል ሊያዳርስ ይችላል፡፡
ለምፅ በአጠቃላይ ጤናችን ላይ የሚያመጣዉ ችግር አለ?
ትልቁ የዚህ በሽታ ችግር የስነ ልቦና ጫና ነዉ፡፡ በሃገራችን ከሐይማታዊ እና ለምፅ እና ባህላዊ አመለካከቶች ጋር በተያያዘ ቆዳ ነጭ ሲሆን እንደ መጥፎ ነገር የማየት ልምድ አለ፡፡ የስነ ልቦናዉ ጫና በጊዜ ካልተገታ በስተቀር ሰዎች በዚሁ ቀላል ምክኒያት አላስፈላጊ የአእምሮ ችግር ዉስጥ ይገባሉ፡፡ ሰዉ ምን ይለኛል ብሎ መሳቀቅ፤ ድብርት፤ ጭንቀት፤ ከማህበረሰብ እራስን ማግለል፤ እራስን ዝቅ አርጎ ማየት፤ ማፈር እና ለመሸፋን መሞከር፤ በስራ ላይ ዉጤታማ አለመሆን፤ እራስን ለመጉዳት መሞከር እና ለተመሳሳይ የስነ ልቦና ጫና ይጋለጣሉ፡፡ ከምንም በላይ ምክር እና የስነ ልቦና ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡
ለምፅ እንዴት ይታከማል?
የሕክምናዉ ዓላማ ቆዳ ዥንጉርጉር እንዳይሆን ለማመሳሰል፤ ወደ ቀድሞ ቀለም ለመመለስ፤ እና እንዳይሰፋ ለማድረግ ነዉ፡፡
- እንደ ሐኪሙ ዉሳኔ መሰረት የተለያዩ የሚቀቡ መድሐኒቶች ሊታዘዙ ይችላሉ፡፡
- የሚዋጡ መድሐኒቶች
- በብርሃን መልክ የሚሰጡ ሕክምናዎች (Phototherapy and photochemotherapy)
- የስነ-ልቦና ሕክምና
- በተለያዩ ሜካፖች መሸፈን (Camouflage therapy)፡- በተለይም በሕክምና አልጠፋ ላለ የለምፅ ዓይነት ይሆናል፤ ለፀጉር - የፀጉር ቀለም፤ ለከንፈር - ቀለም ያለዉ ቻፕስቲክ፤ ለቆዳ - ከቆዳችን ጋር አብሮ የሚሄድ እንደ Dermablend ያሉ ክሬሞችን በመቀባት መሸፈን፤ በMicropigmentation ንቅሳት ከቆዳችን ጋር ማመሳሰል
- በቀዶ ሕክምና ላይኛዉን ቆዳ ወይም የቀለም ሕዋሳት በመዉሰድ ለምፅ ባለዉ ቆዳ ላይ መትከል (Autologous skin grafts)
- ቆዳ ከ50 በመቶ በላይ ነጭ ከሆነ እንደታካሚዉ ምርጫ ሁሉንም ቆዳ ለማመሳሰል በኬሚካል ነጭ ማድረግ
ለምፅን መከላከል ይቻላል?
እስካሁን ባለዉ የሕክምና ሳይንስ ለምፅን ለመከላከል ሊደረግ የሚገባ የመከላከያ መንገድ የለም፡፡ ማንኛዉም ሰዉ በማንኛዉም እድሜ ያለ ምንም የተለየ አጋላጭ ምክኒያት በለምፅ ሊያዝ ይችላል፡፡